Medrek News Conference Prof Beyene Petros

ከፖለቲካ ትርፍ ይልቅ ለሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅሞች ቅድሚያ ይሰጥ! ከመድረክ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጥሮና በሠው/በመንግስት/ሰራሽ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ስትናጥ ቆይታለች፣ አሁንም እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት በየጊዜው በነበሩት አምባገነን መንግስታት የተወሰዱት እርምጃዎች መንግስታቱንና ጥቅሞቻቸውን ማዕከል ያደረጉ እንጂ የሀገሪቱንና የህዝቡን ችግር በመፍታት ላይ ያነጣጠሩ ስላልነበር ለህዝቡ ሲያስገኙ የነበሩት ውጤቶች አነስተኛ እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም የተነሳ ችግሮች በችግሮች ላይ እየተደራረቡ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ምስቅልቅል እያወጡና እያወሳሰቡ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

ከብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ዘግናኝ ደም መፋሰስ በኋላ በ1983 ዓ.ም በትረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የኢህአዴግ መንግስትም የሀገሪቱን ችግር እፈታለሁ በማለት በአፉ ብዙ ቢናገርም በተግባር ግን በሕግ የመግዛት ተግባርን በመከተሉ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ሕዝባችን ላይ ብልሹ የአስተዳደር ሥርዓት ዘርግተው፣ ከ28 ዓመታት በላይ ሲበድሉትና ሲዘርፉት መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በደሉ ያንገሸገሸው ሕዝባችን ያለ ዕረፍት የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ሲታገል ከፍተኛ መስዋዕትነት፡- በእሥራት፣ በስደት፣ በደሙ እና በሕይወቱ ጭምር ከፍሏል፡፡ ይህ የሕዝቡ ትግል ገዝፎ ሥርዓቱን በማስጨነቅ ሊወድቅ እስከሚንገዳገድበት አድርሶት እንደነበር፣ በሂደቱም ከኢሕአዴግ ውስጥ˝የለውጥ ቡድን˝የሚባል ኃይል ተደራጅቶ የበላይ አመራሩን በሌላ እስከሚተካ ድረስ ሕዝባዊ የእምቢታ ትግሉ ውጥረት መፍጠሩ ህዝባችን የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ 

ኢህአዴግ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሾም ለመላው ሕዝባችን የለውጥ ተስፋ ነፀብራቅ የሆኑ እርምጃዎች በመውሰድ፣ በብዙሃን ዘንድ መወደድን ማትረፉ እና ከመድረክና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሂሳዊ ድጋፍ ማግኘቱ፣ ሀገሪቷንና ህዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባትና የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይመራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የዶ/ር አብይ መንግስት፣ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው ኢህአዴግን በብልጽግና ፓርቲ ተክቶ የራሱን ሥልጣን በመደላደል የመጠመዱ ጉዳይ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩልም የለውጥ መንግሥት ነኝ ያለው ኃይል የአስተዳደራዊ መዋቅሩን በ˝ኢሕአዴጋዊ˝ነቱ በማስቀጠሉ፣ የኢሕአዴግ ካድሬዎች እንደነበሩ እንዲቀጥሉ መደረጉ፣  በለውጡ ላይ ከፍተኛ ተስፋ ያደረገውን ሕዝብ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሁሉ እያሳሰበ ይገኛል፡፡ ከዚህም የተነሳ   ዛሬም በሀገራችንና በህዝባችን ላይ የሚከተሉት ሰው ሰረሽ/መንግስት ሰራሽ/ እና የተፋጥሮ ችግሮች መጋረጣቸውን እናስታውላለን፡፡

1.   የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሀገሪቱን ለስጋትና ለፍርሃት ዳርጓት ይገኛል፡፡ ይህ ቫይረስ በዓለም ህብረተሰብ በሞላ ከፍተኛ የሕይወት ስጋት የደቀነ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሕይወቶችንም እየቀጠፈ እንደሚገኝ ዓለም በግልጽ ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ቫይረስ የሚያስከትለውን ስጋት ለመቀነስ እንደ አንድ መፍትሔ የተወሰደው ማህበራዊ መራራቅ እና አካላዊና ትንፋሻዊ ቅርርቦሽን መቀነስ እንደሆነም ዓለም የተግባባበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም በእኛ ሀገር የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በሺህዎችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተለይም በገጠሪቷ የሚኖሩ የገበሬ ካድሬዎቹን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ፖለቲካዊ ሥልጠና ሲሰጡ እያየን ነው፡፡ በእውነቱ ከሆነ ይህ ድርጊት አሳፋሪ ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን ገዥው ፓርቲ ለአርሶ አደርና አርብቶ አደር ህዝባችን ያለውን ከበሬታና ሐዛኔታ አናሳነት የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥ በጣም የዘገየ ቢሆንም በትናንትነው እለት ማለትም መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ይህ ስብሰባ እንዲቀር ውሳኔ እንዳሳለፈ ሰምተናል፡፡

2.   በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የስልክ እና የኢንቴርነት ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ በተለይም በአራቱ የወለጋ የአስተዳደር ዞኖች፣ በሁለቱም የጉጂ የአስተዳደር ዞኖች የስልክና የኢንቴርነት አገልግሎት በአብዘኛው የተቋረጠ ሲሆን በምዕራብ ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በሌሎችም የሀገሪቱ አከባቢዎች የኢንቴርነት አገልግሎት የለም፡፡ ይህ ደግሞ ህዝባችን ስለኮሮና ቫይረስ በሀገርና በዓለም ደረጃ የሚነገሩትን ትምህርታዊና የማስገንዘቢያ ዘመቻዎችን እንዳይሰማ አድርጓል፡፡ አሁን ይህንን መግለጫ እያዘጋጀን ባለንበት ወቅት ለምዕራብ ኦሮሚያ የኢንተርነትና የስልክ አገልግሎት እንደሚለቀቅ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መግለጫ መሰጠቱን ሰምተናል፡፡ ይህ የሚበረታታ እርምጃ ነው እንላለን፡፡ ለወደፊቱም የዚህ ዓይነት ኋላቀር እርምጃ እንዳይደገም እናሳስባለን፡፡

3.   ከመጀመሪያው ያልተፈቱ የትግራይ እና የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፤    በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እንደ አዲስ በውሸት ውንጀላ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባሎችና ደጋፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዋከቡና እየታሠሩ ናቸው፡፡ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ሹሜኞችና የፀጥታ አካላት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን በማሠርና በማስፈራራት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሥራዎቻቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት እየሆኑ ናቸው፡፡ እንዲያውም የወረዳ አመራሮች የተፎካካሪ ፓርቲዎች በወረዳ ደረጃ እንዳይንቀሳቀሱ እንዲከለክሉ መመሪያ እንደተላለፈላቸውም በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የገዥ ፓርቲ አባልና ደጋፊ ያልሆኑ ዜጎች በዘፈቀደ እየተያዙ በወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ይታሠራሉ፤ አሊያም ሥልጠና ተብሎ ወደ ተለያዩ የወታደርና የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋሞች እየተወሰዱ ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኘው፡፡ ስለዚህ መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባሎችንና ደጋፊዎችን ከማሳደድ፣ ከማስፈራራትና ከማሰር እንዲቆጠብ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዓለም በኮረና ቫይሬስ ምክንያት የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ቨይሬሱን ለመከላከል በአንድነት እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የእኛ መንግስትም በፖለቲካ ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች የታሠሩትን ዜጎች በመፍታት ሁሉንም ዜጎች አስተባብሮ ቫይሬሱን በመከላከሉ ሥራ ላይ እንዲያሳመራ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

4.  በግንባታ ላይ ያለው የአባይ ኃይል ማመንጫ ግድብን በሚመለከት ከግብፅ ወገን የሚነሱ ተቃውሞዎች የሀገራችንን ጥቅም የሚፃረሩ እንደመሆናቸው፣ መንግሥት እየተከተለ ያለውን የድርድር አቅጣጫ መድረክ እየደገፈ፣ ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ፣ የትኩረት ቅድሚያ እንዲሰጠው በአንክሮ እናሳስባለን፡፡

5.   በአገራችን በዚህ ዓመት በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት መሃከል፣ ሀገር-አቀፍ ምርጫ ዋነኛው ሲሆን፣ መቼና እንዴት ይካሄድ በሚለው ጉዳይ ላይ በቂ ስምምነት ያለመኖሩ፣ የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት እንዳይኖረው ያሰጋናል፡፡ ከዚህም ሌላ ምርጫ ቦርድ መጪ ምርጫን የሚያስፈጽሙ ምርጫ አስፈጻሚዎችን እየመለመለ እንደሚገኝና እየመለመለ ያለውም ከመንግስት ሠራተኞች እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ከእኛ እውቅና ውጭ መካሄዱንና ከመንግስት ሠራተኞች መሆኑን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ እኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅን ቢሆንም ያቀረብነው ሀሳብ በቦርዱ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱ አሳዝኖናል፡፡ አሁን ከገዥው ፓርቲ እጅ እንበላለን ብለው በሚያስቡት የመንግስት ሠራተኞች መመልመላቸው ከዚህ በፊት የነበረውን የምርጫ ማጭበርበር ታሪክ እንዳይደግም ከፍተኛ ስጋት እንዳለን ከወዲሁ ለሚመለከታቸው አካላት፣ ለህዝባችንና ለዓለም ማህበረሰብ መግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የምርጫው ሂደትና ክንዋኔ ጦርነት መግጠም ይመስል፣ እያንዳንዱ ክልል˝ምርጫውን ለማስፈፀም˝ የሚል ምክንያት እየሰጠ የተለየ የወታደር ኃይል በማሠልጠን ላይ የመገኘቱ ጉዳይ፣ ˝በምርጫው ሂደት በተወዳዳሪዎች መሃከል ግጭት ሊኖር ይችላል˝ የሚል ፍርሃት በሕዝቡ ዘንድ እየቀሰቀሰ በመገኘቱ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሀገሪቷ መቀለብና መሸከም ከምትችለው በላይ ወታደር በየቦታው ማሰልጠን የዴሞክራት መንግስት ባህርይም አይደለም፡፡ መንግስት ዴሞክራት ነኝ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን እየሠራሁ ነኝ እያለ ወታደር የሚያበዛበት ምክንያት አይታየንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በገፍ የሚሰለጥነው ወታደር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚኖረው መንግስት በዚህ በኩል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ቆም ብሎ እንዲመለከት ማስገንዘብ አስፈልጓል፡፡

6.  በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2012 ድንጋጌ ፓርቲዎች ከለጋሾች /ከባለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት አግባብ በአንቀጽ 108 1/ለ መሠረት እንደሚወሰን የተመለከተ ሲሆን፣ ይህ መመሪያ ሳይወጣ ባለሀብቶች ላይ ገዥው ፓርቲ ተጽእኖ በማሳረፍ በቢሊዮኖች ገንዘብ መሰብሰብ የሕግ ጥሰት መሆኑ፤ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ለዓባይ ግድብ ፈጥኖ ማስጨረስ፣ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል እና ለሥራ አጦች ሥራ ፈጠራ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት መደረግ የነበረበት እንደሆነ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልገው የፋይናንስ፣ የባለሙያና የጤና ተቋማት እጥረት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ፣ ያለውን ሀገራዊ ሀብት ገዢው ፓርቲ የራሱን አቅም ለማጎልበት መሰብሰብ መጀመሩ ስህተት መሆኑን መድረክ ያስገነዝባል፡፡  ሕዝባችንም ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

7.   በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ከመንግስት ጋር እየተዋጉ ያሉ   ኃይሎች እንዳሉ እያየን ነው፡፡ ሀገራችን በብዙ የተለያዩ ፈተናዎች ተጋልጣ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት የእርስ በእርስ ጦርነት ከታከለበት ሀገራችንንና ህዝባችንን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ ስለመሆኑ መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መንግስት ከእነዚህ ታጠቂ ኃይሎች ጋር በሠላም የሚነጋገርበት ሁኔታ እንዲፈጠር አበክሮ እንዲሠራ እንጠይቃለን፡፡

8.   በአጠቃላይ መንግስት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው ሕግን አክብረን በመንቀሳቀስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ስንለማመድ ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ በሕገ-መንግስትና ሕገ መንግስቱን በአግባቡ መሠረት አድርገው በወጡ ሌሎች ሕጎች ባለበት ኃላፊነት በመንቀሳቀስ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲፈቱ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና እንዲወጣ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከዚህ በፊት እንደተለመደው ሕገ-መንግስትንና ህግን በመጣስ እቀጥልበታለሁ ብሎ በመሥራቱ ምክንያት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ለሚደርሰው አጠቃላይ ቀውስ ሃላፊነቱ የመንግስትና የመንግስት ብቻ እንደሆነ ከወዲሁ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

9.   ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ሁለንተናዊና አሳሳቢ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻለን  በሰጥቶ መቀበል መርህ /win win agreement approach/ ተቀራርበን እንዲንወያይና እንድንሠራ የትግል ጥሪ እናቀርብላቸዋለን፡፡

10. የተበላሸው የሀገራችን የፖለቲካና የመንግስት አስተዳደር ሀገራችንን ወደ መጥፎ መንገድ ገፍቶ ገፍቶ በአፋፍ ላይ አድርሷት ይገኛል፡፡ ይኸው የተበላሸ መንግስታዊ አስተዳደር ሀገሪቷንና ህዝቦቿን በሁሉም መስክ አቅም በማሳጣቱ የተነሳ የሀገሪቷ የተፈጥሮና ሰውሰራሽ ችግሮችን የመቋቋም አቅምና ኃይል በአነስተኛ ደረጃ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ይህንን የተበላሸ የመንግስት አስተዳደርና ሥርዓት ለመለወጥ የሁሉም ዜጎች የሰከነና በግንዛቤ የታጀበ ጥረት ወሳኝ መሆኑን መድረክ በጽኑ ያምናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መድረክ የሀገሪቱን የፖለቲካና የመንግስት አስተዳደር ችግር ብሎም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ባለው ጥረት ድጋፉን ሳይሰስት እንዲያደርግለት በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

11. በመጨረሻም ህዝባችን በአሁኑ ጊዜ መላውን የዓለም ህዝብ ስጋት ላይ ከጣለው የኮሮና ቫይረስን በሚመለከት የሕክምና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ሌሎች ተዓማኒ ምንጮች የሚያስተላልፉትን የመከላከልና የጥንቃቄ እርምጃዎች በመተግበር ራሱን፣ ቤተሰቡንና ህዝቡን እንድታደግ ምክራችንን መለገስ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩልም የጤና ባለሙያዎች ህብረተሰቡን ከዚህ አደገኛ ወረርሽኝ ለመከላከል ከምን ጊዜም በላይ ዝግጅቶቻችሁን እንድታጠናክሩ ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡

 ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግላችን ግቡን ይመታል!

 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ

 መጋቢት /2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Posted in Announcement, Call to Action, News, Opinion Page, Press Releases.