Medrek News Conference

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ፕሮግራም ዛሬም የፖሊቲካ አማራጭ ነው!

በወቅቱ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መድረክ የተሰጠ አቋም መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የተፈራረቁባትን አምባገነን ሥርዓቶች ለማስወገድ ፈርጀ ብዙ ትግል ስታደርግ ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን በማስተዳደር ላይ የሚገኘዉ  ሥርዓት ምንም እንኳን ከወትሮዉ ፍጹም አምባገነናዊ ባህሪዩ በላዕላይ ደረጃ መለወጥ ቢያሳይም በተግባር ግን ሕዝባችን ዘንድ የደረሰ መሻሻል እያየን አይደለንም። ሥርዓቱ አሁንም የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት መቆጣጠሩንና የመንግስት ዋና ዋና ተቋማትን ለወገናዊ የፓርቲ ዓላማ  ማዋሉን ቀጥሎበታል። እነዚህ ሁኔታዎች ጠንካራና የተባበረ ትግል የሚጠይቁ እንጂ በሚቀርቡ የገዥዉ ቡድን የለዉጥ ትርክቶች ምክንያት መዘንጋት ያለባቸዉ አይደሉም።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የየራሳቸዉ ማንነትና መገለጫዎች ያላቸዉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንደዚሁም የተለያዩ ሀይማኖቶችና እምነቶች ተከታዮች በጋራ የሚኖሩባት ሕብረ ብሔራዊት ሀገር ነች። ይህች የብዝህነት መገለጫ የሆነችዉ ሀገራችን ግን የዜጎችዋ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይከበሩ የብዙሃን መሰቃያና ጥቂት አምባገነን ገዥዎች በየጊዜዉ የሚፈራራረቁባትና የሚንደላቀቁባት ሆና ኖራለች። መድረክ እንደዚህ ዓይነቱን ተለዋዋጭ አምባገነናዊ ሥርዓት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማስወገድ ሀገራችን ወደ ትክክለኛ ሥርዓት እንድትሸጋገርና ሕዝባችንም በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነትን ገንብቶ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ተረጋግጠዉለት፣ የሀገራችን ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ ይታገላል። 

ከዚህም የተነሳ የኢ/ፌ/ዴ/አንድነት መድረክ የሀገራችን መሰረታዊ ችግሮች በሰላማዊ የፖለቲካ ዉድድር አሸንፈዉ በሚወጡ አማራጮች ለመፍታትና የመቻቻል ፖለቲካ ባህልን ለማዳበር የሚያስችልና የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማስፈን እንዲቻል ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል ላይ ይገኛል። መድረክ ዓላማዉን ከግብ ለማድረስ የሚመራበትን  ፕሮግራም ነድፎ በህገ መንግስቱ የሰፈሩት የዜጎች የግል እና የቡድን መብቶች እንዲከበሩ እና ኢትዮጵያ አጽድቃ የተቀበለቻቸዉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መርሆዎቸ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። በተጨማሪም እስካሁንም  ያልተፈቱ በሀገራችን የሚነሱ አንገብጋቢና ዉስብስብ ጥያቄዎች ሁሉን ባለድርሻ አካላትን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሚያሳትፍ መልኩ የሚፈቱበት መንገድ የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ መርሆችን መከተል መሆኑን በአጽናዖት አመላክቷል። 

መድረክ በፕሮግራሙ መስረት እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ምህዳር የፈቀደዉን ያህልና ባገኘዉ ዕድል ሁሉ በመጠቀም በሰላማዊ የትግል ስልት በሀገራችን ኢትዮዽያ  ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ከአስር አመታት በላይ በእጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖም ታግሏል፤ ሕዝባችንንም አታግሏል። መከፈል የሌለበትን መስዋዕትነትም ከፍሏል። በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግሉም ባለፉት ዓመታት ለተካሄዱት የህዝቦች  እምቢተኝነት ትግል በአባል ድርጅቶቹ እና በቀጥታም አመራር በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በዚህም ትግል አስገዳጅነት ገዥዉ ፓርቲ የአመራር ለዉጥ ለማድረግና ለተወሰኑ የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መገደዱ የሚታወስ ነው። ሆኖም የእስካሁኑ የገዥዉ  ቡድን አካሄድ መሰረታዊ የሕግ የበላይነት የማስከበር እና የህዝቦችን ጥያቄዎች ፈጥኖ ለመፍታት ያለዉ ዝግጁነት አናሳ ስለመሆኑ በተግባር የሚታየዉ የሀገራችን አስከፊ ተጨባጭ ሁኔታ ምስክር ነዉ።

የ2012 ምርጫ ተሳትፎን በሚመለከት ”ተሻሻለ” ከተባለው የአዋጅ ረቂቅ ዉስጥ አሳሪ አንቀጾች እንዲወጡ መድረክ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ መንግሥት አዋጁ በችኮላ እንዲጸድ ባደረገበት ሁኔታ፣ ከቀድሞው እጅግ በከፋ ደረጃ ሕግ ሆኖ መውጣቱ የጠበቅነው ለውጥ አልነበረም!  ስለሆነም፣ ማሻሻያ የተባለዉ ቀደም ሲል ባንድ አቅጣጫ ሲወርድ የነበረዉ የምርጫ ጨዋታ እንደዚያው እንዲቀጥል መወሰኑን የሚያመለከት በመሆኑ ትግላችን የሚቀጥል ይሆናል።በተለይም በስልጣን ላይ ያለዉ ገዥዉ ቡድን እዉነተኛ ለዉጥ ለማካሄድ ቆራጠኝነቱ አናሳ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ ከወትሮዉ ትግል መዘናጋት አሁንም አላስፈላጊ ዋጋ ከማስክፈሉ በፊት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ  መታገል ለነገ የማይባል መሆኑን መድረክ ይገነዘባል።

ስለሆነም፣ የሚከተሉትን መርሆች እውን በማድረግ ሀገራችን ያለበትን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር መድረክ ከምን ጊዜም በላይ ይታገላል፦

 1. በአሁኑ ወቅት የግለሰብና የቡድን መብቶችን በአቻነት ማክበር የግድ መሆኑን፣ በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ስለሚያስገድድ፣ በብሔር ብሔረሰብ መብት መከበር እና በኢትዮጵያ አንድነት መካከል ተቃርኖ እንደሌለ ይቀበላል፤ መገንጠልን አይደግፍም፤
 2. ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚኖሩበት መልከአ ምድራዊ ክልል፣ ያለምንም ጣልቃ ገብነት፣ ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳደር መብታቸዉ እንዲከበር   ለዚህም ለበርካታ ውዝግቦች ምክንያት ለሆኑት፣ ለአካባቢ ይገባኛል፣ ለድንበር የማካለል እና ለብሔረሰቦችና የሕዝቦች የማንነት እውቅና ጥያቄዎች፣  በሕገመንግስቱ መሰረት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት፣
 3. በኢህአዴግ  ዴሞክራሲያዊ ማዕክላዊነት መርህ ተሸብቦ የኖረው ፌደራላዊ ስርዓት በትክክል ተግባራዊ እንዲሆንና የሶስቱም የመንግስት አካላት የስልጣን ክፍፍል አንዱ ሌላዉን በሚቆጣጠርበት መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ይሰራል። በፌደራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል የሚኖረዉ የሥልጣን ክፍፍል እና ግንኙነት አንዱ በሌላዉ ሥልጣን ጣልቃ ሳይገባ ሁለቱም በሕገ መንግሥቱ  በተደነገገዉ የሥልጣን ክፍፍል መሠረት የሚሠሩበት ትክክለኛ የፌደራሊዝም መርህ የተከተለና በትክክል ሥራ ላይ የሚዉል እንዲሆን ማድረግ ። በተለይም የፌደራልና የክልል መንግሥታት በየክልሉና በበታች እርከኖች የሚኖሩትን በቁጥር አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዲወጡ ማድረግ፣
 4. ሕገመንግስታዊነትና ዲሞክራሲያዊ  ሕገመንግስታዊ ሥርዓት እንዲጎለብቱ በአሁኑ ወቅት ያለዉ ሕገመንግስት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝቡንም ባሳተፈ መልኩ ዉይይት ተደርጎበት በሕዝበ ዉሳኔ ጭምር የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ፣
 5. ለሀገራችን ዉስብስብ ችግሮች መፍትሔ፣ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለዉን አካል ጨምሮ፣ ሁሉን ባለድርሻዎች የሚያሳትፍ የሀገራዊ መግባባትና የብሄራዊ ዕርቅ መድረክ ለመፍጠር፤
 6. ፍትሃዊነትን በሁሉም የኑሮ እና በኤኮኖሚ ዐውድ ማስፈን፤ በተለይም የኑሮ ውድነትን  ለመቅረፍ የሚያስችሉ ገበያ የማረጋጋት እርምጃዎችን በወሳኝነት ለመውሰድ፣
 7. በአሁኑ ጊዜ በየቦታው ያሉ አክቲቭስቶች እንቅስቃሴ መስመር እንዲይዝ ማድረግ፣
 8. የዜጐችን ህይዎት ባጠፉት፣ባፈናቀሉት እና ቤተ-እምነቶች ላይ ጉዳት ባደረሱት ላይ አስቸኳይ  ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣
 9. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ስቴድዮሞች ከእርስ በርስ ግጭቶች ነፃ እንዲሆኑ ሕግና ስርዓትን ማስከበር፣
 10. ዜጎች በሙያ፣ በጾታ፣ በዕድሜ እና በመሳሰሉት የብዙሀን ማህበራት ከገዥዉ ፓርቲና ከመንግሥት ጥገኝነትና ተጽዕኖ ነጻ ሆነዉ በሲቪክ ማህበርነታቸዉ ለአባሎቻቸዉ ፍላጎትና ጥቅም እንደዚሁም ለህግ ብቻ ተገዥ በመሆን እንዲደራጁና እንዲንቀሳቀሱ ተገቢ ሁኔታዎችን ማመቻቸት 
 11. በኢህአዴግ አገዛዝ አርሶ አደሩ የሚጠቀምባቸዉ መሬቶች ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ እየተሰጡ አርሶ አደሩ በሰበብ አስባቡ ከይዞታዉ የሚፈናቀልበት አሠራር እንዲወገድና ይህንኑ አድሎአዊና ኢሕገመንግስታዊ አሠራራቸዉን ለማክናወን እንዲያስችላቸዉ በየክልሎቹ መንግስታትና በፌደራል መንግሥታት ደረጃ ያወጧቸዉ የመሬት አስተዳደር አዋጆች   እንዲሻሩ ወይም የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲስተካከሉ ማድረግ፣
 12. የከተማ መሬት ግልጽና ከሙስና በጸዳ አግባብ የሚተዳደርበት፣ ነዋሪዎችም ሆኑ አልሚዎች መሬት በተመጣጣኝ ክፍያ የሚያገኙበትና የባለቤትነት መብታቸዉ የሚጠበቅበት፣ አቅም የሌላቸዉ ዜጎች ብድር የሚያገኙበትና መሬታቸዉ ወይም ቤት ንብረታቸዉ ለልማት ሲፈለግ ተመጣጣኝ ካሳ    እንዲከፈላቸዉ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት፣
 13. ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ተንሰራፍተዉ የሚገኙት ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግሮች ዋነኛ ሰለባ ስለሆኑ እየደረሰባቸዉ ያሉትን የሥራ አጥነትንና የኑሮ ዉድነት ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችሉና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መርሀ ግብሮችን በማዉጣት  ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኙ  ወጣቶች የዜኘት መብታቸዉ ተከብሮ በትምህርት ዉጤታቸዉ፣ በሙያ ብቃታቸዉና በክህሎታቸው ብቻ ተወዳድረው ሥራ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠርና ሥራ ለማግኘት ሲሉ በፓርቲ ተጽዕኖ ሥር የሚደራጁበት ሁኔታ ማስወገድ፣
 14. ሴቶች ከወንዶች እኩል ሥራና ክፍያ የማግኘት፣ ሀብት የማፍራት፣ የንብረት ባለቤት የመሆንና የመዉረስና የማዉረስ መብታቸዉ   የእኩልነት መብታቸዉን ለማጎልበት የት የሥልጠና እድሎችን እንዲያገኙ፤ በእርግዝናና በወሊድ ወቅቶችም መብታቸዉ ተጠብቆ በቂ እረፍት የሚያገኙበት ሁኔታን ማመቻቸት፣
 15. በመጨረሻም፣ በየወቅቱ በሀገራችን የፖሊቲካ ምህዳር ላይ የሚነሱት የተለያዩ ጉዳዮች/አጀንዳዎች (“የዜግነት ፖለቲካ”፣ ፌደራሊዝም፣ ሕገ መንግስት ወዘተ)፣ሕዝቦቻችንን ግራ በማያጋቡ መል፣ በሰከነ መንፈስ የጽንፍ ፖለቲካን አስወግዶ በብሄራዊ መግባባትና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓትን በማስፈን ለመፍታት መድረክ ቆርጦ እንደሚታገል መግለፅ እንወዳለን። ዚ    ሲ ሁሉ ሊ ሎ   ቢ   ፈቱ  ።

ድል ለሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግላችን! ሀገራችን ኢትዮዽያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)

ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ።

Posted in Press Releases.