ESDP Banner Showing Diverse Ethiopia

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ማዕከላዊ ም/ቤት አስቸኳይ ስብሰባን ተከትሎ ከፓርቲዉ የተሰጠ መግለጫ

የዜጎችን ሰብዓዊና ሕጋዊ መብቶች፣ ሰላምና ደህንነት ማስከበር የመንግሥት ተቀዳም ተግባር መሆኑ እየተዘነጋ፣ የግጭቶች እና የመከፋፈል ስጋቶች መስፋታቸው ይስተዋላልና መንግስት በአስቸኳይ ሀላፊነቱን መወጣት አለበት!!


ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ


የክልልና የወረዳ ጽ/ቤቶችን በመወከል የተዋቀረው የኢሶዴፓ ማዕከላዊ ም/ቤት፣ በአዲስ አበባ ዋና ጽ/ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የጋራ ግንዛቤ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ብዛት ያላቸው ፓርቲዎች፣ “ርዕዮተ-ዓለማችን ሶሻል ዴሞክራሲ (ማህበራዊ ፍትህ) ነው” ማለትን እንደ አዲስ ግኝት አድርገው፣ በኢትዮዽያ የፖሊቲካ መድረክ ላይ ተንሸራሽሮ የማይታወቅ አዲስ ርዕዮተ-ዓለም በማስመሰል በሚያስተጋቡበት ወቅት፣ ፓርቲያችን ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ ሶሻል ዴሞክራሲን (ማህበራዊ ፍትህን) ርዕዮተ-ዓለሙ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ፣ በ1997 ዓ/ም ምርጫ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች አሸንፎ ፓርላማ እስከ መግባት የደረሰ እንደ መሆኑ፣ ይህንን የቆየ የፖለቲካ መሥመሩን በመላ ሀገሪቱ በማስፋፋት ለበለጠ ውጤት መሥራት እንዳለበት ግንዛቤ ላይ ደርሷል፡፡ለዚህ ዓላማውም ከሌሎች መሰል አመለካከት ካላቸው ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ጋር የመሥራት ተገቢነትን እንደ አቅጣጫ አስቀምጧል።


እስካሁን ያለውን የኢሶዴፓ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመገምገም፣ ፓርቲው በሕዝብ ውስጥ ጎልቶ እንዲወጣ ተከታታይና ሰፊ እንቅስቃሴዎችን በራሱ፣ በኢሶዴፓ ስም፣ ማድረግ እንዳለበት ታምኗል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ፡ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) እንቅስቃሴ ተጠናክሮ በቀጣዩ ምርጫ ሕዝባችንን ለመንግሥት ሥልጣን ባለቤትነት ማብቃት የሚቻለው፣ እያንዳዱ አባል ድርጅት በሚያደርገው ጠንካራ እንቅስቃሴ መሆኑ ተጢኖአል፡፡ መድረክንም ሌሎች ድርጅቶችን በአባልነትም ሆነ በአጋርነት በመጋበዝ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።
እንደዚሁም በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ምህዳር፣ አሁንም እንደወትሮው በኢሕአዴግ ካድሬዎች ቁጥጥር ሥር እንደመሆኑ ለነፃ እንቅስቃሴ የሚመች ያለመሆኑን በብዙ መልክ አይቷል፡፡

ከእነዚህም መካከል “ተሻሻለ” የሚባለው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ይብሱኑ አሳሪ ስለመሆኑ፡ ነባር ፓርቲዎች እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ መደንገጉ፣ ፓርቲዎች ለምዝገባ የሚሰበስቡት የድጋፍ ፊርማ መጠን እጅግ የተጋነነ መሆኑ፣ ፓርቲን በመወከል የሚወዳደሩ ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲሰበስቡ መወሰኑ፣ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ዕጩ ተወዳዳሪ ለመሆን ሥራ ልቀቁ የሚል ጫና መፍጠርን የመሰሉ ድንጋጌዎች፣ በምርጫዎች ላይ የሕዝብን ተሳትፎ የሚገድቡ መሆናቸው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በማጤን፣ በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ማሻሻል እንዲደረግ የሚል አቋም ወስዷል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ውጤት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡


በአገሪቱ መልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ተሸርሽሮ፣ አሁንም በዜጎች ላይ እና ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ስለሆነው ለማንነታቸው መከበር በሚታገሉ ወገኖች ላይ ዘግናኝ የሆኑ የጭካኔ እርምጃዎች፣ በየክልሉ የኢሕአዴግ መንግሥታት እየተፈፀሙ መሆኑ ለሀገሪቱ ህልውና የስጋት ምንጭ እንደሆነ መቀጠሉ አሳስቦናል።
በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጥ እና እርስ በርስ ባላቸው ጥምረት ውስጥ የሚንፀባረቀው ልዩነት፣ ግንባሩ ሀገሪቱን የሚያስተዳድር ቡድን እንደመሆኑ፣ ከፍተኛ የስጋት ምንጭ መሆኑ ተጢኗል፡፡


ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትተዳደረው ባለው ሕገ-መንግሥት እንደመሆኑና የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ማህበራዊ ስብስቦች፣ ግለሰብ አክትቪስቶች እና ኢ-መደበኛ አደራጃጀት ጭምር ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት ሁሉ ፍላጎቶቻቸውን ማቀንቀን ያለባቸው በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑ እየተዘነጋ ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ስሜታዊነትን እየጫረ ያለው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ፣ ከተማው በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር ስር እንደመሆኑ፣ ተገቢነት የሌላቸውንና ወቅቱን ያልጠበቁ የይገባኛል ጥያቄዎች በማንሳት ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚያውኩ ወገኖች ስርዓት እንዲይዙ አሳስቧል፡፡
በሀገሪቱ በስፋት በግለሰቦችና በቡድኖች ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች በሕግ አግባብ ሳይዳኙ እና ተገቢው ካሣና ማስተካከያ እርምጃዎች ሳይደረግባቸው እየቀረ፣ “የዕርቅ ስብሰባ” እየተባለ፣ ሕዝባዊ ተዓማኒነት የሌላቸው ሽማግሌዎችን ጭምር እያሳተፉ “ሰላም አወረድን” እየተባለ፣ በደል አድራሾቹ ሕግ ፊት ሳይቀርቡ እየቀሩ የተበዳዮች መብትና ክብር እየተረገጠ በመሆኑ በአስቸኳ መታረም እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በዚህም ረገድ፣ ሕጋዊ እልባት ያልተሰጠው በቡራዩ ከተማ በጋሞ ብሔረሰብ ሠርቶ-አደሮች ላይ የደረሰው የጭካኔ እርምጃ በምሳሌነት የሚወሰድ፣ መንግሥት ተጠያቂዎችን ያልቀጣ ወንጀል መሆኑ በእጅጉ አሳዝኖታል፡፡


ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ ወደፊትም የሚኖሩ፣ የጋራ እሴቶች እና ተዘማጅ ባህሎች ያሏችው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ክብር፣ ለግልና ለቡድን መብቶችና ነፃነት በጋራ የተዋደቁም ናቸው፡፡ ከግማሽ ምዕተ-ዓለም በላይም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን በጋራ የታገሉ፣ እየታገሉም ያሉ እና ጥለው እየወደቁ የመጡ ፅኑ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ አብሮነትን የሚሸረሽሩ እርምጃዎችና ቅስቀሳዎች መንፀባርቅ መጀመራቸው እና በሁኔታዎቹም ላይ የመንግሥት ዝምታ ኢሶዴፓን በእጅጉ እያሳሰበው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝብ አስተያየትና ሀሳብ እየተረገጠ አምባገነንነት በአንዳንድ ባለሥልጣናትና ወገኖች ጭምር እያቆጠቆጠ መሆኑ እየታየም ነው፡፡


ስለሆነም፣


1. የሕዝባችን አብሮነት፡ የሰላምና የዘላቂ ደህንነት፣ የሉዓላዊ አንድነታችን ዋስትና ስለሆነ፣ መንግሥት ስሕተቶችን አርሞ፣ የሕዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮችን እያዳመጠ፣ የሕዝብ ውሳኔ በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፀባረቅ የፖለቲካ ምህዳሩን በማመቻቸት ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡


2. ሕዝቡ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ፣ አድማሱን በማስፋት በመላ አገራችን ይስፋፋል በሚል እሳቤ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች በመቻል፣ በትዕግሥት እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ፣ ተስፋውን በሚያጨልም ደረጃ አገራችን ወደ አስከፊ ቀውስ እየገባች ትገኛለች፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝባችንንና ታሪካዊ ሀገራችንን ስለማይመጥን፣ እየከሰተ ላለው ቀውስ አስተዋፅዖ እያደረጉ ያሉ ወገኖች ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሀገራዊና ሕዝባዊ ሀላፊነቱን ተገንዝቦ ራሱን እንዲያስተካክል እንጠይቃለን፡፡


3. የአገሪቱ መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶችን ምክክርና መተማመን የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካይነት የተረቀቀውና ለፓርላማ ቀርቦ “የፀደቀው” አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ፣ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር እጅግ መጥበቡን ያሳየ ክስተት ነው፡፡ አዋጁ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን የማሻሻያ ሃሳቦች በተገቢው ያላካተተ መሆኑ ተዓማኒነትንና ግልጸኝነትን አሳጥቶታል፡፡ የሕግ ግድፈቶችም ተስተውለውበታል፡፡ ስለሆነም፣ መንግሥት በአዋጁ ላይ መሻሻል ተደርጎ ነፃ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ ምርጫ እውን የሚሆንበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲፈጥር እንጠይቃለን፡፡


4. በየደረጃው በመንግሥት ሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ባለሥልጣናት የሚፈጽሙት አመጽና ማስፈራሪያ በአባሎቻችን ላይ እያደረሰ ያለው ተፅእኖ፤ በተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ለጽ/ቤት የሚሆን ቤት እንኳን በኪራይ ማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለመጥራት እየተፈጠሩ ያሉ ሳንካዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በእጅጉ ገድበዋል፡፡ ስለሆነም፣ ቀጠዩ ብሔራዊ ምርጫ አሳታፊ፣ ሰላማዊ፣ ታዓማኒና ፍትሐዊ እንዲሆን መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያስተካክል አበክረን እንጠይቃለን፡፡

በሀገራችን ማህበራዊ ፍትህ ዕውን እንዲሆን የምናደገው ትግል ግቡን ይመታል!
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ/ም፣
አዲስ አባባ

Posted in Press Releases.