ESDP Older FB Page Banner Pic

በሰፈራ መርሀ-ግብር አማካይነት መንግሥት ከአንዱ አከባቢ ወደ ሌላ አከባቢ ወስዶ ላሰፈራቸው ዜጎቻችን_ደህንነት_አስተማማኝ_ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል!!!

ከኢትዮጵያ_ሶሻል_ዴሞክራቲክ (ማህበራዊ ፍትህ) #ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

በኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ ከተጎዱ ወይም የመሬት ጥበት ካለባቸው አከባቢዎች ዜጎችን ወደ ለም እና ሰፊ መሬት ወዳለባቸው አከባቢዎች በይፋ ማስፈር የተጀመረው ከፊውዳሉ ሥርዓት ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል::

ይህ ዜጎችን ለረዥም ዓመታት ከቅድመ- አያቶቻቸው ጀምሮ ሲኖሩ ከነበሩበት ቀዬአቸው አስነስተው እንግዳ ወደ ሆነ አከባቢ የማስፈሩ ተግባር ብዙ ጉድለቶች የነበሩበት ሆኖ የቆየ ነው፡፡ከጉድለቶቹም ዋናዎቹ ፡- በቂ ጥናት በሠፈራው አከባቢ ተደርጎ ለሰው መኖሪያነት (ለጤና፣ እርሻ ወዘተ) አመቺነት ያለመጠናት ፤በሠፈራው አከባቢ ነዋሪ ከሆኑ ህዝቦች ውይይት አድርጎ እንግዳ ሰፋሪዎችን ለመቀበልና አብሮ ለመኖር ፈቃደኛነታቸውን በቅድሚያ ያለማረጋገጥ፤ ለሰፈራ ለሚንቀሳቀሰው ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ከነዋሪው የአከባቢ ሕዝብ ጋር በቅድሚያ ያለማስተዋወቅ እና ለሰፋሪው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታን በቅድሚያ ያለማዘጋጀትና ያለማቋቋም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን በነበረው የሰፈራ ዓላማዎች አንዱ ሕዝቡን ከእርስ- በእርስ ጦርነት አከባቢዎች ማስወጣትም እንደነበረ ሲዘገብ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

ይህ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ እና በተገቢው ያልተቀዳ የሰፈራ መርኃ-ግብር፣ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝባችንን መስዋዕትነት ሲያስከፍል ኖሯል፡፡ያለ በቂ መከላከያ ተላላፊ በሽታዎች ወባን ጨምሮ፣ ሰፋሪውን ፈጅቷል፡፡ ሌላው አደጋ ነባሩ ነዋሪ ሕዝብ ሰፋሪውን እንደወራሪ ባዕድ እየቆጠረ ኢ-ሰብአዊ ጥቃቶችን በመሰንዘር ከፍተኛ ጉዳት በሰው ሕይወትና ንብረት መድረሱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደርግ በወደቀ አከባቢ በጋምቤላ የሰፈሩት ወገኖች እንደ የዱር እንስሳት እየታደኑ መገደላቸውና በመተከል /ፓዌ ሰፋሪዎች በቤተክርስቲያን ለአምልኮ በተሰበሰቡበት ተጨፍጭፈው መገደላቸው መራር ትውስታዎች ሆነው እያሉ በእህአዴግ አገዛዝ ዘመንም ሰፋሪው መቀጠሉና በሳፋሪው ሕዝባችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ፈረጀ- ብዙ እየሆነ መቀጠሉ ዜጎችን ለከፍተኛ እንግልትና ሰቆቃ መዳረጉ በእጅጉ ኢሶዴፓን ያሳሰበው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግ ዘመን ልዩ ገጽታው፣ ካድሬዎቹ በዘረኝነትና በጥሰት አጀንዳቸው ተነሳስተው ነባር ነዋሪውን ሕዝብ በሰፋሪው ላይ እያነሳሱ የግዲያ፣ ምዝበራና አከባቢውን ለቀው እንዲፈናቀሉ የሚያሥገድዱ እርምጃዎችን

እያስወሰዱ መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ ያለመሄዱ የዝባችንን ሰብአዊና የዜግነት መብቶች የሚያስከብርና ለደህንነቱ ዋስትና የሚሰጥ መንግሥታዊ ሥርዓት በሀገራችን እንደሌለ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረዥም ዘመናት ደሙን እያፈሰሰ አጥንቱን እየከሰከሰና ሕይወቱን እየገበረ፣የሐገሩን ነጻነት ከወራሪ ሀይሎች እየተከላከለ የሚኖረው ከኢትዮጵያ ሰማይ ጣሪያ በታች በማኝኛውም፣ አከባቢ በህጋዊ ይዞታነት ከተያዘ መሬት ውጭ ያለው መሬት፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ንብረት መሆኑን በመረዳት ነው ፡፡ በወቅቱ ባለው ሕገ-መንግሥት ፣ “መሬት የሕዝብ እና የመንግሥት ነው” ተብሎ የተደነገገው በዚሁ መንፈስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ አከባቢ በሕጋዊ መንገድ ሰፍሮ የመኖር እና ንብረት አፍርቶ ሰላማዊ ሕይወት የመምራት ሕጋዊ መብት ያለው በመሆኑ ማንም ጉልበተኛ ተነስቶ “ ይህ አከባቢ ወይም ይህ መሬት፣ የእኛ ስለሆነ ከሌላ አከባቢ መጥቶ የሰፈረ ሁሉ አከባቢያችንን መልቀቅ አለበት” ብሎ ሁከት መፍጠር፣ ሰፋሪዎችን መግደል፣ በንብረታቸው ላይ ጉዳት ማድረስና ከአከባቢው ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡

ይህ ጤነኛ አመለካከት ጠፍቶ ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙት ሕገ ወጥ እርምጃዎች ሲቆጨን ከቅርብ ወራት አንስቶ በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ መንግሥት ከቤት ንብረታቸው አስነስቶ ባሰፈራቸው ከከምባታና ጠምባሮ በመጡ ዜጎች ላይ ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ አከባቢያችንን ለቃችሁ ውጡልን በሚል ዛቻ የታጀበ ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው ቢቆይም መንግሥት ለነዚህ ወገኖቻችን ጥበቃ በማድረግ ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ሲገባው እንደዋዛ ተመልክቶ አልፎታል፡፡ በመሆኑም በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት “በጫካ የሚኖሩ ዘላኖች” ናቸው የሚላቸው ሕገወጥ ሀይሎች “መሬታችንን መልሱልን ” በማለት በሰፋሪው ላይ ባካሄዱት የጥቃት ዘመቻ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ 37 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውንና ከ20‚ 000 በላይ ሰፋሪዎች መፈናቀላቸውን ከአከባቢው ከደረሰን መረጃ ማወቅ ችለናል፡፡ መንግሥት ለነዚህ ከሰላማዊ ኑሯቸው አፈናቅሎ “የተሻለ ኑሮ ትኖራላችሁ” በማለት ላሰፈራቸው ዜጎች ሌላው ቢቀር ደህንነታቸውን እንኳን ማረጋገጥ ያለመቻሉ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሌላው አስገራም ጉዳይ ከሰፈሩበት ተፈናቅለው መጥተው በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና ከተማ ዱራሜ ላይ ያለ መጠለያ ሜዳ ላይ ተበትነው ለተፈናቃይ ዜጎች የሚቀርበው የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ያለመደረጉ መንግሥትን ለትዝብት የዳረገው ጉዳይ ነውና የኢህአዴግ መንግሥት ይህንን መሠረታዊ ሃላፊነት ሳይወጣ ቀርቶ ተፈናቃዩን ወገኖች ገና ሲጀመር “ መሬት ጠቦ መተዳደሪያ አጣችሁ ”በማለት ወዳስነሳቸው የቀድሞ ቀዬአቸው ተመለሱ በማለት እየወሰደ ያለው እርምጃም ሃላፊነት የጎደለው እንደመሆኑ በአጽንኦት እናወግዛለን፡፡ መንግሥት ይህን በተፈናቃይ የከምባታ ጠምባሮ ወገኖቻችን ላይየደረሰውን የወንጀል እርምጃ ተከታትሎ ወንጀለኞቹ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እንዲሰጥ፣ መልሶም እንዲያቋቁማቸው እና ለደረሰባቸው ጉዳት ካሣ እንዲከፍል በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

በአሁኑ ወቅት እየደረሰ ያለው ዜጎች በተለያዩ መንስኤዎች ምክንያትነት የመፈናቀል ሁኔታ የሰፋ እንደመሆኑ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችና ብሔራዊ ከበርቴዎችም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በሰፋሪ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግዲያና ማፈናቀል ከአንዱ አከባቢ ወደ ሌላ አከባቢ የመዛመት ባሕሪ ያለው በመሆኑ በሌሎች፤ አከባቢዎች በሚገኙ ሰፋሪ ዜጎቻችን ላይም የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ከመድረሱ በፊት፣ መንግሥት በሁሉም አከባቢዎች የሰፈሩ ዜጎቻችን ሕይወት ላይ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ተገንዝቦ የዜጎቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ ገለልተኛ እና አስተማማኝ የጥበቃ ሃይል በአስቸኳይ እንዲመደብ በአጽንኦት እናሳስባለን፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክቲክ ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)

ጥር 16/ 2011

አዲስ አበባ

Posted in News, Opinion Page, Press Releases.