Prof. Beyene Petros Interview 1

በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸሙ ያሉት አሰቃቂ ጥቃቶች በአስቸኳይ ሊገቱ ይገባል

(ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)
ባለፉት የኢህአዴግ አገዛዝ ዓመታት ዜጎቻችን በብሔር ብሔረሰብ ማንነታቸው ምክንያት በተለያዩ የሀገራችን
አከባቢዎች የተለያዩ ጥቃቶች እየደረሱባቸው ከመኖሪያቸውና ከሥራ ቦታዎቻቸውም እየተፈናቀሉ በገዛ ሀገራቸው
ለስደትና ለእንግሊት ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ
ዜጎቻችን በመላ ሀገራችን የዚሁ አይነት ጥቃቶች ሰለባዎች ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ኢሶዴፓ እንደዚህ አይነቶቹ ጥቃቶች
እንዲቆሙና የዜጎቻችን ሰላምና ደህንነት የሚረጋገጥበት እርምጃዎች በመንግሥት በኩል እንዲወሰዱ በተደጋጋሚ
ሲያሳስብ የቆየ ቢሆንም እስከ አሁን ችግሮቹ ከመባባሳቸው በስተቀር ተጨባጭ መፍትሔ ሲሰጥላቸው አልታየም፡፡
በዚሁም መሠረት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቤንሻጉል ጉሚዝ ነዋሪ በነበሩት የኦሮሞ ብሔር አባላትና  በሌሎችም
የተለያዩ ብሔረሰቦች አባላት ላይ ከባድ መሳሪያዎችን በታጠቁ አጥቂዎች ግዲያዎችና የማፈናቀል እርምጃዎች ተወስደው
ከመቶ በላይ ዜጎቻችን ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ሊቆስሉ ችለዋል፡፡ ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎቻችንም ከቤት ንብረታቸው
ተፈናቅለው በአቅራቢያው በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም በመስከረም 17 ቀን
2011 ዓ ም በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በአምስት ቀበሌዎች ሲኖሩ በነበሩ የከምባታና የጠምባሮ ብሔረሰቦች አባላት
ላይ ከደቡብ ሱዳን ድንበር አከባቢዎች ከሜኑትና ከጫራ ብሔረሰቦች የመጡ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃቶች ከ25 ሰዎች
በላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ጊዲያዎች የተፈጸሙባቸው ሲሆን በርካቶች ከመቁሰላቸውም በላይ የቤት እንሰሳትና በርካታ
ሌሎች ንብረቶቻቸው ተዘርፎባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀልና
ለስደት ለመዳረግ ተገደዋል፡፡ ቀደም ሲልም በዚሁ በመስከረም ወር  ውስጥ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ክልል ነዋሪ በሆኑና ለብዙ ዘመናት አብረው በሰላም ሲኖሩ በነበሩት የመስቃንና ማረቆ ብሔረሰቦች መካከል በድንበር
አካለል ጉዳይ ምክንያት በመስቃን ወረዳ በኢንሳኖ ከተማ በተነሳው አለመግባባት ግጭት ተነስቶ ከሁለቱም ብሔረሰቦች
አባላት 14 ሰዎች ለሞት፣ ከ20 በላይ ሰዎች ደግሞ ለመቁሰል የተዳረጉ ሲሆን ከ6,000 የሚበልጡ ዜጎቻችን
ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ 12 ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች በውስጡ ከነበሩ ንብረቶች ጋር
ሲቃጠሉ አንድ መኪናና ወፍጮም ተቃጥሎአል፡፡ በድምሩም ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሊወድም
እንደቻለም ከአከባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ ከዚህም ሌላ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትና
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ወሰኖች አከባቢ በሚኖሩት በጉጂ ኦሮሞና በቡርጂ ብሔረሰብ፣ እንደዚሁም
በጉጂ ኦሮሞና በኮሬ ብሔረሰብ መካከል ተቀስቅሶ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና እስከ አሁንም የቀጠለው ግጭት
ለብዙ ዜጎች ሕይወት መጥፋትና ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደም  እያስከተለ ቢሆንም መፍተሔ ሳይሰጠው ለረጅም
ጊዜ በመቆየቱ የአከባቢውን ሕዝብ ለከፍተኛ ስቃይ ዳርጎት ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ ጥቃቶች በሀገራችን በርካታ አከባቢዎች እየተለመዱ መምጣታቸውና
በዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ ጎዳቶች እያስከተሉ መሆናቸው እንደዚሁም በመንግሥት በኩል ችግሮቹ እየታወቁ እነዚህን
ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች ለማስቆም የሚያስችሉ ወቅታዊና ተመጠጣኝ እርምጃዎች በመንግሥት በኩል አለመወሰዳቸው
የሕዝባችን ሰላምና ደህንነት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባና የሕግ የበላይነት የሌለበት ሁኔታ በሀገራችን መፈጠሩ
የኢህአዴግ አገዛዝ መንግስታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን አመላካች ናቸው፡፡
ስለዚህም መንግሥት፡-
1ኛ፡- በዜጎቻችን ላይ በፀረ-ሰላም ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን በአስቸኳይ በማሰቆምና ዜጎቻችን ዘላቂ
ሰላም የሚያገኙበትና ደህንነታቸው የሚረጋገጥበትን ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስድ፡
2ኛ፡- በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ የሚገኙት ወንጀለኞች በሕግ ፊት ቀርበው በሕግ ተጠያቂዎች እንዲደረጉ፣
3ኛ፡- በእነዚሁ ጥቃቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትና ልዩ ልዩ ጉዳቶች የደረሱባቸው ወገኖቻችን ተመልሰው
የሚቋቋሙበትና ሰላማዊ ኑሮአቸውን የሚመሩበት ሁኔታዎች በአስቸኳይ እንዲመቻቹላቸው፣
4ኛ- ለግጭቶቹ ምክንያት እየሆኑ ያሉት መሠረታዊ ችግሮችም በአግባቡ ተጠንተው ዘላቂ መፍትሔ
እንዲሰጣቸው፣አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
መንግሥት ለሕዝባችን ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ቅዲሚያና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ
መስከረም 28 ቀን 2011
አዲስ አበባ
Posted in Press Releases.

2 Comments

  1. how much the leading party believe the comptants to work together & to take any measure on terror activists…….

  2. It’s good. Please organize press conference on conflict between Mareko and Meskan people conflict in Guragae Zone which lefts more than 50 individual deaths, many casualities and nearly 40, 000 people displacement. Still the government is not ready to solve the causes of the problems (9 kebeles issues).

Comments are closed.