በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የኢሶዴፓ መግለጫ

በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስኬታማና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በብሔራዊ መግባባትና በሕጋዊና በተቋማዊ
ማሻሸያዎች ላይ ሊመሠረት ይገባል፡፡

(ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ዓመታት እየተፈራረቁ የገዙዋቸው ፊውዳላዊና አምባገነን ገዥዎች በጫኑባቸው አስከፊ
ሥርዓቶች ምክንያት በጋራ የሚፈልጉትን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የበለጸገች
የጋራ ሀገር መገንባት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ሀገራችንን ሲገዛ የቆየው
ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-አንድነት የሆነው የኢህአዴግ አገዛዝ በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው የሀገራችን ብሔር
ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እርሰበርስ የሚጋጩበትንና የሚፋጠጡበትን ሁኔታ ፈጥሮ ሀገራችንን የእርሰበርስ ግጭት፣
የሕይወትና የሀብት ውድመት፣ እንደዚሁም በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የህዝቦች መፈናቀልና ስደት
በተከታታይ የሚታዩባት ብቻ ሳትሆን ሀገራዊ አንድነታችን ሳይቀር የጥፋት ጫፍ ላይ እንዲደርስ አድርጎት ነበር፡፡
ይህን ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ አንድነትና ሥርዓት መርሆዎች ጋር በማይጣጣምና በሚቃረን ሁኔታ ሲካሄድ የቆየውን
የኢህአዴግ አገዛዝ ከፋፋይና በታኝ አቅጣጫ አደገኛነቱን የተረዱ የሀገራችን ፖለቲከኞችና ሰፊው ሕዝብ የአገዛዙን
አያያዝ ከመጀመሪያው የሥልጣን ጊዜው ጀምሮ ሲቃወሙና ሲታገሉ የኖሩ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ የሕዝቡ
የተቃውሞ ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሎአል፡፡ ይህንኑ እውኔታ የተመለከቱት የኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ
የኢህአዴግን ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ ትተው የሕዝባችንን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሀሳብ መጋራት
ከመጀመራቸውም በላይ የኢህአዴግን የአመራር ኃላፊነት ጭምር ይዘው አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ
የለውጥ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ በዶ/ር አቢይ አሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው አዲሱ የኢህአዴግ
አመራር እስከ አሁን በወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ላከናወናቸው ተግባራቱ ከብዙ
የሀገራችን ዜጎች እውቅናና ምስጋና ማግኘቱም የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትራችንና በአጋሮቻቸው እየተገለጹ ያሉትና የሕዝባችንን ልባዊ ፍላጎት የሚያንጸባርቁ
እነዚሁ ቀና የአንድነትና የመደመር ሀሳቦች እስከ አሁን የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና በስደት ላይ የነበሩ
ዜጎቻችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና አክትቭስቶችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ እንደዚሁም ከጎሮቤቶቻችን
ጋር የነበረንን ጤናማ ያልሆኑ ግንኙነቶችን በማሻሻል ረገድ በተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች መደገፋቸው
ከአምባገነናዊ አገዛዝ ለመላቀቅ ላለን ፍላጎት ተስፋ የሚፈነጥቁ ተግባራት ቢሆኑም ሰፊው ሕዝባችን ሲታገልለት
ለቆየው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተማማኝ መሠረት መጣሉን የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡

በፖለቲካው ረገድ ባለፉት 27 ዓመታት ከቆየንበት የኢህዴግ ከፋፋይና የማስመሰል ፖለቲካ ወጥተን ቀና የሆኑ
የሕዝባችንን አንድነትና ትብብሮችን የሚያበረታቱ ሀሳቦችን ከመሪዎቻችን ለመስማት የበቃን ቢሆንም እውነተኛና
ዘላቂነት ያለውን የፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሥርዓት በሀገራችን እውን ለማድረግ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ
ሕጋዊና ተቋማዊ ሥራዎችን በመሥራት ረገድ በአሁኑ ወቅተ ብዙ ይቀረናል ብቻ ሳይሆን ገና ወደ አስተማማኝና
ዘላቂነት ያለው ተግባር አልገባንም ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በጠቅላይ ሚኒስትራችንና አብሮአቸው ከተሰለፉ
የመንግሥት መሪዎች ከተነገሩን ተስፋ ሰጪ ቃላቶችና እጅግ ከሮ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ከሚጠቅሙና
ለቀጠዩ የጋራ ሥራችን መነሻና መተማመኛ ለመሆን ሊያገለግሉ ከሚችሉ አዎንታዊ እርምጃዎች ባሻገር የሀገራችንንና
የሕዝባችንን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ተቃርቦ ከነበረው አምባገነናዊና ከፋፋይ ሥርዓት ወደ ትክክለኛ
ዴሞክራሲያዊና የሀገራችንና የሕዝባችንን አንድነት በቀጣይነት እያጠናከረ ሊሄድ ወደ ሚያስችል ሥርዓት ሊያሸጋግሩን
የሚያበቁ ውይይቶችንና ድርድሮችን ማካሄድና ስምምነቶች ላይ መድረስ እስከ አሁን ገና አልተጀመሩም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥና ተቃዋሚ ሳይሆኑ ተፎካካሪዎች ሊሆኑ ይገባል የሚል ቀና ሀሳብ በጠቅላይ ሚኒስትራችን
የተነገረን ቢሆንም ከገዥነትና ከተቃዋሚነት ወደ ተፎካካሪነት የሚያሸጋግረን ሂደትና ሥርዓት እንዴት ተግባራዊ
እንደሚሆን በግልጽ የተቀመጠ ነገርም የለም፡፡ የኢህአዴጎች ገዥነትና የእኛም ተቃዋሚነት የተከሰተው በአጋጣሚ
ወይም በአባባል ስህተት ሳይሆን በኢህአዴጎች የአገዛዝ ዘመን ኢህአዴጎች ገዥ ሆነው ለረጅም ጊዜ ለመቀጠል
በቀየሱት ሥርዓትና እኛም ይህንኑ የገዥነት አስተሳሰባቸውንና የዘረጉትን የአፈና ሥርዓት ለመቃወምና ለመታገል
ወስነን ሲናከሄድ በቆየነው እንቅስቃሴ ስለነበረ ገዥነትና ተቃዋሚነት እንዲቀር ከንግግርና ከጊዜያዊ የማረጋጋት
ሥራዎች ባሻገር የአገዛዝ ሥርዓትን ከመሠረቱ አስወግዶ የተፎካካሪነት ሥርዓትን እውን ማድረግን ይጠይቃል፡፡
ለዚህም በጥልቀት መደራደርና ነፃ የውድድር ሜዳ መፍጠርን፣ ከገዥው ፓርቲ የተለየ አማራጭ ሀሳብ የሚያራምዱ
ፓርቲዎች እንደ እንጄራ ልጅ ከዚያም አልፎ እንደ ጠላት በመፈረጅ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ጥቃቶች ለመፈጸም
ሲያገለግሉ የቆዩ የአፈና ሕጎችና ተቋማት ላይ ትክክለኛና ተጨባጭ ማሻሻያዎችን ማድረግና ጠንካራና ገለልተኛ የሆኑ
የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን መገንባት ይገባል፡፡ ከዚህም ሌላ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አድልኦ በሌለበት
ፍትሐዊ አይን ተመልክቶ ተገቢውን ድጋፍ ያለፖለቲካዊ ወገንተኝነት የሚሰጥበትና የሚያበረታታበት ሥርዓት መፍጠርና
ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ እነዚህን ተጨባጭ ተግባራት ሳያከናውኑ ከገዥነትና ከተቃዋሚነት ለመውጣትና
ተፎካካሪ ተብሎ ለመጠራት ማሰብ ከመልካም ምኞት የማያልፍ አባባል ብቻ ሆኖ ሊቀር ስለሚችል ቀና ሀሳቡ ወደ መሬት
ወርዶ ተግባራዊ የሚሆንበት ሂደት በተጨባጭ ሊኖር ይገባል፡፡

በኢህአዴግ አገዛዝ ዓመታት ሕዝባችን ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ሲታገል ከቆየባቸው አበይት ጉዳዮች አንዱና
ዋነኛው በሀገራችን የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤትነቱ በትክክል የሚረጋገጥበት ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ እውን
የሚሆንበት ሁኔታ እንዲመቻችለት ነው፡፡ አገዛዙ ምርጫ እያካሄድኩ ነኝ እያለ ጊዜንና የሀገር ሀብትን በከንቱ
ሲያባክን የቆየባቸው ሂደቶች በሙሉ በሕዝባችን ዘንድ ታአማኒነት የሌላቸው ፋይዳ ብስ ሙከራዎች መሆናቸውን
ኢህአዴግ መቶ በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኔንና አጋሮቼን መረጠ ብሎ ሲኩራራ በነበረበት የ2007 ምርጫ ማግስት
ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዙ አይወክለኛም ብሎ ከዳር እስከ ዳር ባቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ በተግባር
አሳይቶአል፡፡ ሕዝባችን ከአሁን በኋላ እንደዚህ አይነት ፌዝና የፖለቲካ ቀልድ ለመሸከም ፈጽሞ እንዳልተዘጋጀም
በማያሻማ ቋንቋ በተግባር ግልጽ መልዕክት አስተላልፎአል፡፡

ስለዚህም በሀገራችን ከአሁን በኋላ በሚካሄዱ ምርጫዎች ሂደትና የምርጫ አስተዳደር ጉዳይ ገዥው ፓርቲ ለደርድር
ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ከሚገኘውና ኢሶዴፓም አባሉ ከሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ
አንድነት መድረክና ከሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር በአስቸኳይ በመደራደር
ከስምምነት ላይ መድረስና ፍትሐዊና ታአማንነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በጊዜ
ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን እንዲሆን ሊያደርጉ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሳይመቻቹ
ዴሞክራሲያዊ ምርጫን መጠበቅ ስለማይቻል ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ በማድረግም በአሁኑ ወቅት ኢህዴግንና መንግሥትን
እየመራ ያለውና በዶ/ር አቢይ የሚመራው አካል የሕዝባችንን የሥልጣን ባለቤትነት ጥያቄ በትክክል ለመመለስ ያለውን
ዝግጁነት በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡

የኢህዴግ አገዛዝ ባለፉት ጊዜያት የሕዝባችንን አብሮነትና አንድነቱን ሲሸረሽር የቆየበትን ሂደትና የህዝባችንን
ግንኙነት የጥላቻና የግጭት ያደረገበትን ሁኔታ ከመሠረቱ በመቀየር በእኩልነት፣ በመከባበርና በፍቅር አብረን
የምንኖርበትን ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አንድነት በመገንባት ረገድም ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ጥሩና ቀና የሆኑ
ሀሳቦች በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲነገሩ መቆየታቸውና በተለያዩ አከባቢዎች ተከስተው የነበሩ አስከፊ ግጭቶችን
ለማረጋጋት የተደረጉት ጥረቶች በአዎንታዊነት የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቶቹና ውድመቶቹ የተከሰቱት
በድንገትና በአጋጣሚ ሳይሆኑ ከአገዛዙ የከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲዎችና ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ባሕሪይ የመነጩ ስለሆኑ
በሥርዓቱ ሕጎችና ፖሊሲዎች እንደዚሁም የአገዛዝ መዋቅሩ ላይ ተጨባጭ ማሻሸያዎችና ለውጦች ሳይደረጉ ቀና ሀሳቦችን
በመናገርና በጊዜያዊ የማረጋጋት ሙከራዎች ብቻ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ስለዚህም የችግሮቹን መንስኤዎች
ከሥር መሠረቱ ማጥናትና ትክክለኛ መፍትሔ በማግኘት ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው ብሎ ኢሶዴፓ ያምናል፡፡

በሀገራችን የተጀመረው ለውጥም ከሁሉ በፊት ይህንን የሀገራችንና የሕዝባችንን ሕልውና አደጋ ላይ ጥሎ የቆየውን
ሁኔታ በመቀየርና ዘላቂነት ያለው መፍትሔ በማስገኘት ችግሩን ማስወገድን ጊዜ የማይሰጠው ቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ
ይገባል፡፡ የለውጡን ዓላማዎች በስውር የሚቃወሙና ለውጡን ዋጋ ለማሳጣት የሚሹ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት ተጨማሪና
አዳዲስ ግጭቶች በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንዲከሰቱና የሕዝባችን መልካም ግንኙነትና የሀገራችን አንድነት
አደጋ ላይ እንዲወድቁ፣ ሕዝቡም በለውጡ ሂደት ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ እየተፍጨረጨሩ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ
ለሕዝባችን ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነትና አንድነት የሚሠራው ሥራ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግሩንም
ገዥው ፓርቲ በየአከባቢው በሚገኙ ካድሬዎቹ አማካይነት ብቻ ለመፍታት እያደረገው ያለው ሙከራም አጥጋቢ ውጤት
እያስገኘ አይደለም፡፡ ስለዚህም ነው ኢሶዴፓ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
በኢህአዴግ አገዛዝ ሀገራችን የገባችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በጥልቀት በመመርመር አምባገነናዊ አገዛዙን ወደ
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላማዊ አግባብ ለማሸጋገር ሁሉም የድርሻውን የሚወጣበት የብሔራዊ አንድነት መንግሥት
ማቋቋም እንደሚገባ በፖለቲካ ፕሮግራሙ በግልጽ ያስቀመጠውና ለኢህአዴግ ባቀረበው የድርድር ሀሳብም በድርድር
አጀንዳነት ያስቀመጠው፡፡ በዚህ መሠረት የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሕገመንግሥታዊ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ መፍትሔ
እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ድርደሮችን ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሰፊው ሕዝብ ጋር በማድረግ ዘላቅነት ያለው
መፍትሔ ካልተገኘለት የሕዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና የሀገራችን ሕልውናም ከተጋረጠባቸው አደጋዎች ለመከላከልና
የምንጠብቀውን ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ አስቸጋሪ ስለሚሆን ለእነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ሕጋዊና
ተቋማዊ መፍትሔዎችን በድርድር በማስገኘት በሁላችንም የጋራ ተሳትፎና ትብብር የለውጡ ሂደት ስኬታማና ዘላቅነት
ያለው እንዲሆን በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተግባራዊ እርምጃዎች በወቅቱ ሊወሰዱ እንደሚገባ
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ያምናል፡፡ በዚሁም መሠረት፡-

1ኛ፡- በሀገራችን መሠረታዊ በሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እጅግ የተራራቁ ሀሳቦችን የሚያራምዱ ኃይሎች የሀሳብ
ልዩነቶቻቸውን ለማቀራረብና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚያከሄዱም ሆነ በምን ዓይነት
ሁኔታ አማራጭ ሀሳቦቻቸውን ለሕዝቡ አቅርበው በሕዝብ ውሳኔ እልባት እንዲያገኝ እንደሚያደርጉ የተቀመጠ የፖለቲካ
አካሄድ ወይም አቅጣጫ እስከ አሁን በግልጽ ስላልተቀመጠና ተግባራዊ እንቅስቃሴም በወቅቱ እየተካሄደ ባለመሆኑ
በሀገራችን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተገቢ ድርድሮች ተካሄደው በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚደረስበት፣
እንደዚሁም በልዩነት በሚቀመጡ ጉዳዮች ላይ በሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ እልባት የሚሰጥበት ሂደት በአስቸኳይ
እንዲጀመር፡፡

2ኛ፡- በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የተሳካና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን የማድረጉ ሂደት በአንድ ፓርቲ
ካድሬዎች አመራር ብቻ ማሳካት እጅግ አስቸጋሪና የማያዋጣ መሆኑ በተግባር እየታየ ስለሆነ የሚመለከታቸው የፖለቲካ
ኃሎች ድርሻቸውን በአግባቡ ሊወጡ የሚችሉበት የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ተመሥርቶ የለውጡ ሂደት የሚመራበት
ሁኔታ እንዲመቻች፡፡

3ኛ፡- በሀገራችን ቀጣይ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት ስለምርጫ አስተዳደር፣ ስለምርጫ ውድድር ሂደቶችና ስለነፃና
ገለልተኛ ታዛቢዎች በአጠቃላይም ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማንነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ለማካሄድ በሚያስችሉ
ጉዳዮች ላይ ተገቢው ድርድር ተደርጎ ከስምምነት ላይ እንዲደረስና ይኼው ተግባራዊ የሚሆንበት የሕግና የአሰራር
ሁኔታዎች እንዲመቻቹ፡፡

4ኛ፡- በሀገራችን በሕጋዊ አግባብ ተመዝግበው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎችና
አባሎቻቸው ሕጋዊ የዜግነት መብታቸው ተከብሮ ከገዥው ፓርቲ፣ ከአጋሮቹና ከአባሎቻቸው ጋር በእኩልነት ታይተው
ከእንቅስቃሴያቸው ጋር የሚመጣጠን ተገቢውን አገልግሎትና ፍትሐዊና ሕጋዊ ድጋፍ ከመንግሥት የሚያገኙበት ሁኔታም
በአስቸኳይ እንዲመቻችና ተግባራዊ እንዲደረግ፡፡

5ኛ፡- በብሔር ብሔረሰብ ማንነታቸውና በእምነታቸው ምክንያት በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች አስከፊ ጥቃቶች
እየተፈጸሙባቸው ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ለአሰቃቂ ኑሮ የተዳረጉት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ወገኖቻችን ወደ
ቀድሞ አከባቢያቸውና ኑሮአቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበትና ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም አግኝተው የሚኖሩበት ሁኔታዎችም
በአስቸኳይ ተመቻችተው ተግባራዊ እንዲደረጉ፡፡

6ኛ፡- በኢህአዴግ አገዛዝ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ
ሲፈጸሙ የቆዩት ጥቃቶች በብዙ አከባቢዎች ( ለምሳሌም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎችና ወሰኖች አከባቢዎች፣
በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወሰኖች በተለይም በጌድኦ፣ በቡርጂ፣ በኮሬ፣ በሲዳማና በወላይታ
ብሔሮችና ብሔረሰቦች አከባቢዎች፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ወሰን አከባቢዎች፣ በአማራና በቤንሻንጉል ጉምዙ
ክልሎች ወዘተ) በለውጡ ሂደትም ያላቋረጡና የብዙ ዜጎች ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ክስተቶች እየተከሰቱ
በመሆናቸው ሕዝባችን በሰላም ኑሮውን ለመምራትም ሆነ በነፃ ከቦታ ወደ ቦታ ለመዘዋወር የሚችልበት አስተማማኝ
ሁኔታ ገና አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህም በሰላማዊ ዜጎች ላይ በየሥራ ቦታዎችና በየመንገዱ ጥቃት በማድረስ ላይ
በሚገኙት ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃዎች በመውሰድ የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት
እንዲሁም የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ድል ለሰላማዊና ሕዝባዊ ትግላችን፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ

መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ ም

አዲስ አበባ

Posted in News, Opinion Page, Press Releases.