Welcome to Ethiopia Sign

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እንኳን ለሚትወዱዋት ሀገራችሁና ለሰላማዊ ትግሉ አበቃችሁ ይላል

በውጭ ሀገር በስደት ፖለቲካና በትጥቅ ትግል ተሰማርተው የቆዩ ወገኖቻችንን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በደስታ
ከመቀበል ባሻገር በሀገራችን የኃይልና የስደት ፖለቲካ ለዘለቄታው እንዲያበቃ ከልብ መሥራት ይኖርብናል፡፡

(ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

አምባገነናዊ ፖሊሲዎችን የሚከተሉ አገዛዞች ባሉባቸው ሀገሮች ከገዥዎቹ የተለየ አማራጭ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች
ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለፍትሐዊ የአስተዳደር ሥርዓት ያላቸውን አማራጭ ሀሳቦች
በሰላማዊ አግባብ ለማቅረብም ሆነ በሕዝቡ ነፃ ምርጫ ውሳኔ እንዲያገኝ የማድረግ መብታቸው በአገዛዞቹ የኃይል
እርምጃዎች መታፈንና ሕልውናቸውም አደጋ ላይ መውደቅ ወይም ለብዙ ሲቃዮችና እንግሊቶች መዳረግን ስለሚያስከትል
ዜጎች በስደት ፖለቲካና የትጥቅ ትግል አማራጭ ውስጥ መግባታቸው በፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች ሥር ባሉ ሀገሮች
የሚታይ እውኔታ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቦቹዋም በአምባገነናዊ አገዛዞች ሲገዙ ለረጅም ዓመታት የቆዩ
በመሆናቸው የስደት ፖለቲካና የትጥቅ ትግል ለብዙ ዜጎችዋ በአምባገነን ገዥዎች የተጫኑባቸው ግዴታዎች ሆነው
ቆይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሰደው የስደት ፖለቲካዊ
እንቅስቃሴዎችንና የትጥቅ ትግሎችን ሲያካሄዱ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኖ ቆይቶአል፡፡

ባለፉት የኢህአዴግ አገዛዝ ጊዜያት በስደት ፖለቲካና በትጥቅ ትግል ተሰማርተው የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ወደ
ሀገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ በሚካሄዱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ አስፈላጊው ሁኔታዎች በመንግሥት
በኩል እንዲመቻቹና የስደት ፖለቲካና የትጥቅ ትግል አስፈላጊና ግዴታ የሚሆንበት የፖለቲካ ምህዳር ከሀገራችን
ተወግዶ ሁሉም በሰላማዊ አግባብ አማራጮችን ለሰፊው ሕዝብ እያቀረበ በነፃ የሕዝብ ምርጫ እልባት የሚያገኙበት
አሰራሮች እውን እንዲሆኑ በሰላማዊ ትግል ላይ ተሰማርተው የቆዩት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ያላሰለሰና ያላቋረጠ ትግል ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት
መድረክ አባል የሆነን የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክን በመሠረትንበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ እንደ መሠረታዊ
መርሆአችንና የትኩረት አቅጣጫችን ወስደን በጋራ የፖለቲካ ፕሮግራማችን በግልጽ በማስፈር ለተፈጻሚነቱ ሲንታገል
ቆይተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይኼው ሕዝባዊ ትግላችን ፍሬ አፍርቶ በስደት ፖለቲካና በትጥቅ ትግል ላይ ተሰማርተው
የቆዩት ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስና በሰላማዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ በመብቃታቸው የኢትዮጵያ ሶሻል
ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ እየገለጸ ከስደት ፖለቲካና ከትጥቅ ትግሉ ተመልሰው ሰላማዊ ትግሉን
በሀገራቸው ምድር ለማካሄድ ለበቁት ወገኖቻችን እንኳ ለሚትወዱዋት ሀገራችሁና ለሰላማዊ ትግሉ አበቃችሁ በማለት
ወገናዊ የደስታ መግለጫ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

በኢሶዴፓ እምነት አሁን የተገኘው ውጤት የብዙ ጊዜ የትግል ውጤትና የሀገራችን ፖለቲካ አንድ እርምጃ ወደ ፊት
ያራመደ ክስተት ቢሆንም ለዘላቂነቱ ግን ብዙ መሠራት የሚገባቸው ሥራዎች ከፍታችን ተደቅነው ይገኛሉ፡፡ በዚሁም
መሠረት፡-

1ኛ፡- በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታየ ያለውን ሕዝባዊ የለውጥ ፍላጎትና ጠንካራ የትግል እንቅስቃሴ በመቀበልና
በመደገፍ አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ የሚገኘውና በዶ/ር አቢይ አሕመድ የሚመራው የሀገራችን
መንግስት በስደት ፖለቲካና በትጥቅ ትግል ላይ ተሰማርተው የቆዩ ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸውና ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ
እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥሪ ከማስተላለፍና ሲመለሱም አቀባበል ከማድረግ ባሻገር ለወደ ፊቱም ዜጎችን ወደ ስደት
ፖለቲካና ወደ ትጥቅ ትግል የሚገፉ ሁኔታዎች በሀገራችን እንዳይኖሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭነት ያላቸውና
በሕግና በተግባርም የሚረጋገጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህም ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው ዜጎች
ስለሀገራቸውና ስለሕዝባቸው ያላቸውን አማራጭ ሀሳቦች በነፃነትና በሰላማዊ አግባብ በማቅረባቸውና በአማራጭ
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመሳተፋቸው በአሸባርነትና በጥፋት ኃይልነት በመፈረጅ በመንግሥት ሲፈጸሚባቸው የነበሩትን
የተለያዩ ጥቃቶችን የሚገታና አጥቂዎችን በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን
የሚያስከብርና የሕግ የበላይነትን እውን የሚያደርግ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመድረስ ደግሞ
ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ጊዜ ሳያጠፉ መደራደርና እስከ አሁን የነበሩትን የሕግና የአሰራር ሁኔታዎችን
በማሻሻልና በመለወጥ አጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩን መሠረታዊ በሆነ ደረጃ መለወጥ ይገባል፡፡

2ኛ፡- በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራቸውና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመመለስ ላይ የሚገኙት ወገኖቻችንም በሙሉ
ልባቸው ሰላማዊ የትግል አማራጭንና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን እውን ለማድረግ በርትተው መሥራትና በሀገር ውስጥ
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በከፍተኛ ትዕግስት እልህ አስጨራሹን ሰላማዊ ትግል ሲያካሄዱ ከቆዩት ተቃዋሚ የፖለቲካ
ፓርቲዎችና ከምልዓተ-ሕዝቡ ጋር ትግላቸውን በማስተባበርና በማቀናጀት ይህ አሁን የተገኘው አዎንታዊ ሁኔታ
ዘላቂነት ያለው እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ ይገባቸዋል፡፡ ኢሶዴፓ እንኳን ለሀገራችሁ በሰላም በቃችሁ
ከማለት ባሻገር ከሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን በሁሉም የሀገራችን ጉዳዮች ከእናንተ ጋር
ለመወያየትና በሚያግባቡን የሀገራችንና የሕዝባችን ጉዳዮች ሁሉ ከሁላችሁም ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን
ያረጋግጣል፡፡

3ኛ፡- ይህ በሀገራችን እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ሲታገሉ የቆዩት ሰላማዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ
ፓርቲዎችና ምልዐተ- ሕዝቡም አሁን የተከሰተው አዎንታዊ ሁኔታ ዘላቂነት ያለው ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ሁኔታ
በአስተማማኝነት እስኪረጋገጥና የኃይልና የስደት ፖለቲካ ከሀገራችን ጠፍቶ ወደ ታሪክ እስኪቀየር ድረስ እስከ
አሁን ሲያካሄዱ የቆዩትን የየበኩላቸውን ጥረቶች አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ በዚህም ያላሰለሰ የጋራና የተቀናጀ
ጥረት ሀገራችን ከኃልና ከስደት ፖለቲካ ተላቃ ዜጎች አማራጭ ሀሳቦቻቸውን በሀገራቸው ውስጥ በነፃነት እያራመዱና
ሰላማዊ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ እንቅስቃሴዎችን እያካሄዱ በሰላም የሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንዲትሆን
ማድረግ ይጠበቅብናልና ሁላችንም የድርሻችንን እንዲናበረክት ኢሶዴፓ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ድል ለሰላማዊና ሕዝባዊ ትግላችን፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ

ጳጉሜ 3 ቀን 2010

አዲስ አበባ

Posted in News, Opinion Page, Press Releases.