ሰላማዊ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ማስፈራራት የፀረ- ዴሞክራሲያዊነትና የሽብርተኝነት ተግባር ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን

(ዶ/ር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ስልጣን ከያዙ ወዲህ እየወሰዱ ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች ለመደገፍ
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ ም በመስቀል አደባባይ በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ
ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገራዊ ጉዳዮች ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ የፈለገውን የመደገፍና ያልፈለገውን የመቃወም ሰብአዊና
ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ለማስከበር ለዘመናት ሲታገል ኖሮ ይኼው መብቱ በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መረጋገጡ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ይኼው መብት በትክክል በተግባር ላይ እንዳይውል ተደርጎ ለ27 የኢህአዴግ አገዛዝ ዓመታት ታፍኖ
በመቆየቱ ትዕግሥቱ የተሟጠጠበት ሕዝባችን ባለፉት 3 ዓመታት ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን ለማስከበር ሀገር አቀፍ
የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማድረግ በእልህ አስጨራሽና መራር ትግል ውስጥ ገብቶ ሕይወቱን ጨምሮ በርካታ
መስዋዕትነቶችን ሲከፍል ቆይቶአል፡፡

ዶ/ር አቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ባሉት ሶስት ወራት ያህል ጊዜ አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎች
በመወሰዳቸው የተደሰተው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የአዲስ አበባ ከተማና የአከባቢው ሕዝብ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ
ም የተጀመሩትን አዎንታዊ እርምጃዎች ለመደገፍና ለማበረታታት በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ በማካሄድ
ላይ እያለ ይህንኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ለማደናቀፍ በተነሳሱ ኃይሎች የእጅ ቦምብ ተወርውሮ የሁለት ሰው
ሕይወት ሲጠፋ ከ160 በላይ ዜጎቻችን የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት
መድረክ በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች
መጽናናትን፣ የመቁሰል አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ደግሞ ፈውስና ብርታትን ይመኛል፡፡

መድረክ ይህ አስጸያፊ የሆነው የፀረ-ዴሞክራሲ ኃይሎች ድርጊት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተግባራዊነት ቆርጦ
የተነሳውን ሕዝባችንን ከጽኑ አቋሙና ትግሉ ቅንጣት ታህል ወደ ኋላ እንደ ማይመልሰው ያለውን ጽኑ እምነት
እየገለጸ፣ የፀረ-ዴሞክራሲና የአሸባርነት ተግባራቸውን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብም በብሔር
ብሔረሰብም ሆነ በማንኛውም ሌላ ሁኔታ ሳይከፋፈልና ለካፋፋይ ኃይሎች አንዳች ቀዳዳ ሳይሰጥ በሰላማዊ አግባብ
የመደገፍም ሆነ የመቃወም ሰብአዊ ና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ለማስከበርና ይህንኑ መብቶቹን የሚጻረሩ ኃይሎችን
በአንድነት ለመመከትና ለመታገል በርትቶ ለበለጠ ትግል እንዲንቀሳቀስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አሁን በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ውጤታማ ሆኖ ባለፉት 27 ዓመታት ሰፍኖ የቆየው ፀረ- ዴሞክራሲያዊ
ሁኔታ እንዲለወጥና ዘላቂ መፍትሔዎችም እውን እንዲሆኑ ለማድረግ መድረክ ከኢህአዴግ ጋር የጀመረውን ድርድር
በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሎ በበኩሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡

ድል ለሰላማዊና ሕዝባዊ ትግላችን!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/
ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ ም
አዲስ አበባ
Download pdf.

Posted in News, Opinion Page, Press Releases, Questions & Answers.